ለኢይዝራኤሉ ሰው ለናቡቴ በሰማርያው ንጉሥ በአክዓብ ቤት (ቤተ መንግሥት) አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው። አክዓብም ናቡቴን፦
“ለቤቴ ቅርብ ነውና የተክል ቦታ ይሆነኝ ዘንድ ይህንን የወይን ቦታህን ስጠኝ፥ ከሱ የሚበልጥ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፥ ዋጋውንም
ትወድ እንደሆነ የዚህን የወይንህን ቦታ ወርቅ እሰጥሃለሁ፥ የተክል ቦታ ይሁነኝ፤” አለው። “ወይቤሎ ናቡቴ ለአክዓብ ኢያምጽእ ሊተ
እግዚአብሔር ከመ አሀብከ ርስተ አበውየ። ናቡቴም አክዓብን የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እንዲህ ያለ ነገር (ክፉውን ኅሊና)
እግዚአብሔር አያምጣብኝ፤” ሲል መለሰለት፡ ናቡቴ ይኽንን የመለሰው፦ “ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም በእኔ ፊት እንግዶችና መጻተኞች
ናችሁና ምድርን ለዘለዓለም አትሽጡ።” በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርቶ ነው። ዘሌ ፳፭፥ ፳፫።
Tuesday, February 26, 2013
Sunday, February 3, 2013
“ሢመት፤”
ሢመት፦ ሹመት፥ ሥልጣን፥ ማዕርግ ማለት ነው። የሚሾም፥ የሚሸልም፥ የሚያሠለጥን፥ የሚቀድስ፥ የሚያከብር ደግሞ እግዚአብሔር
ነው። የይሁዳ ገዢ ጲላጦስ፦ ጌታችንን፦ “ልሰቅልህ ሥልጣን እንደ አለኝ፥ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንደ አለኝ አታውቅምን?” ባለው
ጊዜ፥ “ከሰማይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህም፤” ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፱፥፲-፲፩።
Tuesday, January 22, 2013
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፮
ሥዕል፦ ከክርስትና በፊት ሥዕል በቤተ አሕዛብም ሆነ በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር። በቤተ
አሕዛብ እንጨት ጠርቦ ደንጊያ አለዝቦ ማምለክ የተለመደ ነበር። እንዲያውም የሮማ ነገሥታት አማልክት ተብለው ከመመለካቸው በላይ
ከሞቱ በኋላ ሥዕላቸው በደንጊያና በእንጨት እየተቀረጸ ሲመለኩ መኖራቸው በታሪክ ይታወቃል። ክርስትና በመጣ ጊዜም ከክርስትና ጋር
ያጣላቸው ይኸው ልማዳቸው ነው። በክርስትና ትምህርት ይህ አምልኮ ጣዖት ነውና፤ በቤተ አይሁድም እንደ አሕዛብ ሳይሆን በታቦተ ሕጉ
በጽላተ ኪዳኑ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሥል ራሱ እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት ነበር። ዘጸ 25፥19። ነገሥ ቀዳ 6፥23። ሕዝ 9፥3፣
10፥3፣ 10፥1። ሔኖ 14፥11 ዘጸ 25፥20፤ ዘፍ 3፥24። እነዚህ የኪሩቤል ሥዕሎች ከታቦቱ አይለዩም። ምክንያቱም ታቦት የእግዚአብሔር
መገለጫ ዙፋን ስለሆነ የመንበረ ፀባዖት አምሳል ነው። ሥዕለ ኪሩቤልም የጸወርተ መንበር ኪሩቤል አምሳል ነውና፥ የሚሳሉትም እንደሚናተፍ
አውራ ዶሮ ሁነው ነው። የንጉሥ አንጋች ንጉሡ በተቀመጠበት በዙፋኑ ፊት ነቃ፥ ቆጣ፥ ብሎ እንደሚቆም።
Wednesday, December 26, 2012
“ዘይሁብ መርሐ ርቱዓ ለቤተክርስቲያን”
በጸሎተ ኪዳን ዘሠርክ ላይ እንደተነገረው፥
ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ ለምትሆን፥ ጸጋን ኃይልን ለምታድል፥ አምነው ለሚቀርቡት ምስጋና አንድም በሃይማኖት ለሚገኝ ክብር ማረፊያ
ማሳረፊያ ላደረጋት ለቤተክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። የተገረፈላት፥ሥጋውን የቆረሰላት፥ ደሙን ያፈሰሰላት፦ ነፍሱንም
አሣልፎ የሰጠላት እርሱ ነውና። የሐዋ ፳፥፳፰።
ጥንት ሙሴን እና አሮንን ልጆቹንም ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የመረጠ
እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፫፥፩-፳፪፣ ፳፰፥፩-፲፬ ። ይህንን ምርጫ ለመቃወም ወይም በምርጫው ጣልቃ ለመግባት የሞከሩ ዳታን፥ ቆሬንና
አቤሮን ፍጻሜያቸው አላማረም። “እናንተ የሌዊ ልጆች ስሙኝ፤ የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር ለይቶ የመረጣችሁን የእግዚአብሔርን
ድንኳን አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ እንድታገለግሏቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁን ታሳንሱ ታላችሁን?” ብሎ
የመከራቸውን ሙሴን አልሰሙትምና ዘኁ ፲፮፥፩-፶። ከቤተ መንግስቱም ሰዎች እነ ዖዝያን እግዚአብሔር የመረጣቸውን ገፍተው ቤተ መቅደሱን
ደፍረው ነበር። “ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፥ በዕጣን መሠዊያውም ላይ ያጥን ዘንድ
ወደ መቅደስ ገባ ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን
እየተቃወሙ፥ ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን ለተቀደሱት ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ አይገባህም፥ ከእግዚአብሔር
ርቀሃልና ከመቅደሱ ውጣ፥ ይህ በአም ላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ክብር አይሆንህም፥አሉት፤” ይላል። የንጉሡም መጨረሻ አላማረም።
፪ኛ ዜና ፳፮፥፲፮-፳፫
Monday, December 17, 2012
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፭
በእንተ ታቦት
ታቦት፦ ከብሉይ ኪዳንና ከእሥራኤል የነፃነት ሕይወት ጋር የተያያዘ
ታሪክና የት መጣ አለው። ታሪኩና የት መጣው የታወቀ ቢሆንም ለመግቢያ ያህል በመጠኑ ከዚህም እናነሣለን። እሥራኤል በግብፅ ለአራት
መቶ ሠላሳ ዓመታት ያህል በባርነት ቀንበር ሲገዙ ከኖሩ በኋላ በሙሴ መሪነት በእግዚአብሔር ተአምራት ከግብፃውያን የአገዛዝ ቀንበር
ነፃ ወጡ።ወደ አገራቸውም ለመመለስ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሀ ሲኳትኑ ኖሩ። በግዞት ሳሉም ሆነ አሁን በጉዟቸው ከአባቶቻቸው
የወረሱትን ሃይማኖት አልረሱም። “ የአብርሃም ፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብም አምላክ፤” አድነን ፥ ፍረድልን ከማለት አቋርጠው አያውቁም
ነበር። ይህን ጽኑ እምነታቸውንና በስሙ ስለተጠሩ የሚደርስባቸውን ሥቃይና ግፍ ተመልክቶ ነፃ አወጣቸው። ነፃ ካወጣቸውም በኋላ በድብቅ
በግዞት ያቀርቡ የነበረውን አምልኮት ነፃ ሕዝብ ሁነው በነፃ እንዲያመልኩት ራሱ ስለፈለገ፥ በዚያው ሲጓዙበት በነበረው በረሀ ውስጥ
በምትገኝ በሲና ኮረብታ ላይ ለመሪያቸው ለሙሴ ተገልጦ የወለባ የቃል ኪዳንና የመታዘዝ ምልክት የሚሆኑ አሥር ሕግጋትና ትእዛዛት
የተጻፈባቸው ሁለት የዕብነ በረድ ገበታዎችን (ሠሌዳዎችን) ሰጠው። ለእሱም ማስቀመጫ ታቦትና እንደ መቅደስም የምታገለግል የምስክር
ድንኳን እንዲሠራ ሙሴን አዘዘው ዘጸ ፳፬፥፲፪፤ ፲፭፥፲፰፤ ፳፭፥፲፣፳፪። ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው። ታቦት ዘጸ ፳፭፥፲፣ ዘሌ ፲፮፥፲፪። ምናልባትም በግዕዝ አወጣጥ “ቤተ፥ አደረ፤”
ከሚለው ግሥ የወጣ ሳይሆን አይቀርም። የታቦት ትርጓሜው ማደሪያ፥ መሠወሪያ ማለት ብቻ ሳይሆን መታያ፥ መገለጫም ነው። ንጉሥ በዙፋኑ
እንዲገኝ፥ እንዲገለጥ፥ ታቦት ለእሥራኤል የአምላክ መገለጫ ነውና። እሥራኤል በጉዟቸው ሁሉ ታቦት ይዘው ሲጓዙ የኖሩት፥ እነ ሰሎሞን
ለታቦቱ የሚሆን ቤተ መቅደስን በከፍተኛ ወጭ ያሠሩትና ለታቦት ይሰግዱ፥ ይንበረከኩ የነበረው፥ በታቦቱ ውስጥ በነበረው በጽላቱ ዐሠርቱ
ቃላት ስለተጻፉ ብቻ አልነበረም። እሥራኤል ኃጢአት ሠርተው አምላካቸውን ባስቀየሙት ጊዜ በአባር፥ በቸነፈር፥ በምርኮ፥ በጦር ይቀጣቸዋል።
ንስሐ ሲገቡና ሲለምኑት ደግሞ አባት ለልጁ እንደሚራራ ራርቶ ይምራቸው ነበር። የእግዚአብሔር ምሕረት እንደመጣላቸው የሚያውቁትም
በታቦቱ ላይ ብርህት ደመና መጥታ ስታርፍ ነበር። ይህንንም ዕብራውያን “ሸኺናሐ፤” ይሉታል፤ ለምሕረት መገለጥ፥ ለምሕረት መምጣት ማለት ነው።
Sunday, December 9, 2012
“በውኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን ?”
ይኽንን ኃይለ ቃል በቀቢጸ ተስፋ የተናገረው የአማሌቃውያን ንጉሥ አጋግ ነው። አማሌቃውያን ከዔሳው የልጅ ልጅ ከአማሌቅ የተገኙ ነገዶች ናቸው። ዘፍ ፴፮ ፥፲፪ ኑሮአቸው ከእሥራኤል አገር በስተደቡብ ነበር። ከነቢያት አለቃ ከሙሴ ጀምሮ እስከ ንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ድረስ እስራኤልን ይቃወሙ ነበር። “አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል
ጋር በራፊድ ተዋጋ። ሙሴም ኢያሱን፦ ጐልማሶችን ለአንተ ምረጥ፥ ሲነጋም ወጥተህ ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፥ እኔም በተራራው ራስ ላይ
እቆማለሁ፥ የእግዚአብሔርም በትር በእጄ ናት፥ አለው። ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ወጥቶም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮን
ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። እንዲህም ሆነ፥ ሙሴ እጁን በአነሣ ጊዜ (በአምሳለ መስቀል እጆቹን ግራና ቀኝ በዘረጋ ጊዜ) እስራኤል
ድል ያደርግ ነበር፥ ደክሞትም እጁን በአወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር። ድንጋይም ወሰዱ፥
በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፥ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፥ ፀሐይም እስክትገባ
ድረስ እጆቹ ተዘርግተው ነበር። ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ።” ይላል። ዘጸ ፲፯፥፰-፲፫። (ሙሴ በአምሳለ መስቀል
እጆቹን ዘርግቶ በእሥራኤል ዘሥጋ ኃይል መንፈሳዊን አሳድሮባቸው ድልን እንዳጐናጸፋቸው፦ እኛም በመስቀሉ ኃይል በአጋንንት ላይ ድልን
እንጐናጸፋለን)።
Sunday, December 2, 2012
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፬
የቅዱሳን መላእክት ክብርና ምልጃ፤
የምልጃ ትምህርት ሐዋርያዊ ውርስ (Apostolic
succession) ባላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የታወቀና የሚሠራበት ነው። ቅዱሳን መላእክት ረቂቃን ፍጥረታት ናቸው። በእግዚአብሔርም
ፊት በባለሟልነት የሚቆሙ ናቸው። ሉቃ ፩፥፲፱። የእግዚአብሔርን ኃይል ለመግለጥ የሚላኩ ናቸው። ኢያ ፭፥፲፫-፲፭። የእግዚአብሔርን
ምሕረትና ይቅርታ ለሰው ልጅ፥ የሰውን ልጅ ትሩፋትና ማናኛውንም በጎ ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ናቸው። የሐዋ ሥራ ፲፥፫፣
ዕብ ፩፥፲፭። ከዚህም ሁሉ ጋር በክርስትና ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር ምሥጢር ተካፋዮችና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው። በመጀመሪያ
አምላክ ሰው ሊሆን ነው ብሎ የምሥራች የተናገረ የእግዚአብሔር መልአክ ነው። ሉቃ ፩፥፳፮። በተወለደም ጊዜ የዓለም መድኃኒት ተወለደ
ብሎ መጀመሪያ ለሰው የሰበከው መልአክ ነው። ሉቃ ፪፥፰። የሕፃኑን መሢህ ሕይወት ለማጥፋት እነ ሄሮድስ ያጠመዱትን ወጥመድ በመግለጥ፥
ድንግል እመቤታችን እና ዮሴፍ ወደ ምድረ ግብፅ እንዲሸሹ ያደረጉ መላእክት መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ መዝግቦታል። ማቴ ፪፥፲፫።
Subscribe to:
Posts (Atom)






